በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የተጠናቀቁ ግንባታ ፕሮጀክቶች ምረቃ ተካሄደ፡፡

በምረቃው አዳዲስ ለሚሰሩ ግንባታዎች የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ስርዓት እና እየተሰሩ ያሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ህንጻ እና የተማሪዎች ማደሪያ እንዲሁም የሱታና ኢንተርፕራይዝ ኮምባይነር ምረቃ የተደረገ ሲሆን አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለመስራት የብሄረሰብ አስተዳደሩ እና የዩነቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

በዕለቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ/ር)ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎትን ዕውን ለማድረግ እና ልቆ ለመውጣት የተለያዩ ፋሲሊቲዎችን የማሟላት ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው የተቋም ግንባታ ሂደት ያለ በመሆኑ ባለፉት ዓመታት ሰርቶ ያጠናቀቃቸውን ግንባታዎች ለማስመረቀቅ እና የዩኒቨርሲቲውን የትኩረት መስኮችን ለማሳካት የሚያግዙ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ የዛሬው መርሐ ግብር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ጋርዳቸው አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በዛሬው ዕለት የአስተዳደር ህንጻ፣ የተማሪዎች መኝታ እና ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ግብርናን ለማዘመን የሚያግዝ አንድ ኮምባይነር በመግዛት ማህበረሰቡን ለማገዝ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቀጣይ ለቱሪዝም እና ስራ ፈጠራ (ቱሪዝም ኮንፈረንስ) ሊሆን የሚችል በአይነቱ ልዩ የሆነ እና በ20 ሽህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ እና ከ9 ሽህ በላይ ተሳታፊዎችን በአንዴ ሊያስተናግድ የሚችል “ኦዲተሪየም” ሁለገብ አዳራሽ፣ የአገው ባህል፣ ታሪክ እና ቋንቋን ለማሳደግ እና ጥናት ለማድረግ የሚያግዝ የአገው ጥናት ኢንስቲቲዩት ዘመናዊ አዳራሽ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ እዚህ ቦታ ላይ እንዲመሰረት እና እውን አስተዋጽኦ ያደረጉ የሀገር ሽማግሎች፣ የቀድመው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ብርሀኑ በላይን፣ የዩኒቨርሲቲውን ም/ፕሬዝዳንቶች እና የዩኒቨርሲቲውን ሰራተኞች በሙሉ አመሰግነዋል፡፡

በዕለቱ የተገኙት የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳደሪ አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፈጣን ዕድገት፣ የልህቀት፣ የውጤታማ አመራር ቅብብሎሽ ተምሳሌት መሆኑን አውስተው ዩኒቨርሲቲው ነገን ዛሬ እየሰራ የሚገኝ አይናችን እና የዓይን ብሌናችን እንዲሁም የህዝባችን መገለጫ በመሆኑ ሁላችንም የመጠበቅ እና ዓለም አቀፍ ተቋም እንዲሆን የመስራት ግዴታ አለብን ብለዋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ አክለውም የአገው ህዝብ የጥንታዊ ስልጣኔ እና ታሪክ ባለቤት በመሆኑ ይህን የሚያጠና የሚያሳድግ እና ለትውልድ የሚያስተለልፉ ተቋም ለመገንባት መሰረተ ድንጋይ በማስቀመጥና ለመሰራት ያደረገው ሂደት እጅግ የሚያስደስት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሚፈልጋቸው በተለይም ራሱን የቻለ የሆስፒታል ግንባታ ለሚያስፈልገው የቦታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዩኒቨርሲቲው በሚያቀርብላቸው ጥናት መሰረት ቦታውን ለመሰጠት እሳቸው እና የብሄረሰብ አስተዳሩ አመራሮች ቁርጠኛ መሆናቸውንም አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ ስለእንጅባራ ዩኒቨርሲተ አጠቃላይ የግንባታ ፕሮጀክት ገላጻ ያቀረቡት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር መንግስቱ ሙሉ ዩኒቨርሲቲው እስከ አሁን ድረስ በተለያዩ ምዕራፎች ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸው በዚህ ዓመት የተጀመሩ ከ8ሽህ በላይ ተማሪዎችን በአንዴ የሚያስተናግድ የመማሪያ ክፍል፣ ሁለገብ ዘመናዊ አዳራሽ ፣የአስተዳደር ካፍቴሪያዎች፣ 2 ዘመናዊ የመምህራን የመኖሪያ አፓርታማዎችን እየገነቡ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡

ከተሳታፊዎችም የተለያዩ ሀሳብ እና አስተያየቶች ተሰጥተው በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጋርዳቸው ምላሽ እና ማብራሪያ ተሠጥባቸዋል፡፡ የመምህራን መኖሪያ አፓርታማ ግንባታ፣ የመማሪያ ክፍል ግንባታ እና የግቢ ውስጥ ጉብኝት መርሃግብርም ተካሂዷል፡፡ በመጨረሻም ዛሬ ለተመረቁት ህንጻዎች ጉልህ አስተዋጽኦ ለነበራቸው ለጥላሁን ዋሴ ጠቅላላ ተቋራጭ፣ ለእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አንጅነር መንግስቱ ሙሉ እና ለሲቪል መሀንዲሱ ኢንጅነር ዮሴፍ ማሙሸት የምስክር ወረቀት እና የጃኖ ነጠላ ሥጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *